in

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ! || የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፋሲካ መልእክት

[ad_1]

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ስናስብ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ክህደት፣ ሤራና ፍርደ ገምድልነት ለጊዜው ያሸነፉ ቢመስሉም በመጨረሻ እንደሚሸነፉ ነው። ትንሣኤው ተበስሮ እውነትና ደግነት ድል አድርገው እስኪታዩ ድረስ፣ ክፋትና ውሸት እንደ ቋጥኝ ገዝፈው ታይተዋል፣ እንደ ተራራ የማይነቀነቁ ሆነው ቆይተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የአራት ወገኖችን ሤራ ያፈረሰ ነው። በቃሉ ትምህርት በእጁ ተአምራት ያልተደሰቱ፤ የአዳምን ጥፋት እንጂ የአዳምን ድኅነት የማይፈልጉ፤ በእነርሱ መንገድ ካልሆነ በቀር ምንም ነገር ለመቀበል ፈቃደኞች ያልሆኑ አራት ወገኖች የሠሩት ወጥመድ በትንሣኤው ተወግዷል። የሤራው ጠንሳሽ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ነው። እርሱ የሰው ልጆች የጥንት ጠላታቸው ነው። ምንም ቢሆን በሰው ልጆች ላይ ያለውን አቋም አይቀይርም። የሰው ልጆች እርሱ በሚፈልገው የክፋትና የስሕተት መንገድ ቢሄዱለት እንኳን፣ ለሰው ልጅ ጠላት መሆኑን አይቀይረውም። ዓላማው የሰውን ልጅ ማጥፋት እንጂ ከሰው ልጅ ጋር ወዳጅነት መፍጠር አይደለምና።

የሰውን ልጅ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የታቀዱ የጥፋት ወጥመዶችን ሁሉ የዘረጋው፣ አባሪ ተባባሪ ፈልጎ ሰውን ከፈጣሪው ለመለየት፣ ሰውን እርስ በርሱ ለማጋጨት፣ ኑሮውንም የጨለማና የመከራ ለማድረግ ሲሠራ የኖረው ዲያብሎስ ነው። ብዙ ጊዜ ግን እርሱ በግልጥ አይታይም። አሠራሩንና አካሄዱን የሚያውቁ፤ የሐሰትና የክፋት አባት መሆኑን የተረዱ፤ የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት መሆኑን የተገነዘቡ ብቻ ተንኮሉንና ክፋቱን ያውቁበታል። ሌሎች ግን እርሱ ባጠመደው ወጥመድ ወድቀው ከገዛ ወገኖቻቸው ጋር ሲጋጩና ሲፋጩ ይገኛሉ። ጦሩን ከሚሰብቀውና ቀስቱን ከሚወረውረው ጋር ሳይሆን፣ ከቀስቱና ከጦሩ ጋር ይገጥማሉ።

ዲያብሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሦስት ተላላኪዎችን አሠማርቶ ነበር። እነዚህ ሦስት ተላላኪዎች ከዚያ ቀን በፊት እርስ በርሳቸው የማይስማሙ፤ አንድ ዕቅድ ዐቅደው፣ አንድ ሥራ ሠርተው፣ ለአንድ ግብ ሊሠማሩ የማይችሉ ናቸው። ዲያብሎስ ያደረገው አንድ ነገር ነው። የጋራ ጠላት ፈጠረላቸው። የጋራ ዓላማ ግን አልፈጠረላቸውም። ጠላታቸውን የሚያጠፉበት ምክንያት የተለያየ ነው። ጠላታቸውን ለማጥፋት ያላቸው ፍላጎት ግን አንድ ነው።

ዲያብሎስ ሦስቱን ሲያሠማራ የራሱ ዓላማ ነበረው። እርሱም የሰው ልጅን ድኅነት ማስቀረት ነው። ሦስቱም ተላላኪዎች ሳያውቁት የዚህ ዓላማ ፈጻሚዎች ናቸው። እነርሱ ግን ለየራሳቸው ዓላማ የተሠማሩ መስሏቸው ነበር። የሚገርመው ነገር፣ በመጨረሻ ሦስቱም ተላላኪዎች ጠፍተዋል። ቢሸነፍም ያልጠፋው የላካቸው ዲያብሎስ ነው። ምንጊዜም የጥፋት ተላላኪ ዕጣ ፈንታው ይሄ ነውና።

ዲያብሎስ የአዳምን ድኅነት ለማስቀረትና በምድር ላይ ብቸኛ ገዥ ሆኖ ለመኖር ሦስት አካላትን ለጥፋት አሠማራ። ይሁዳ፣ የአይሁድ ካህናትና ሮማውያን። ይሁዳ ዓላማው ገንዘብ ነው። ገንዘብ እስከሰጡት ድረስ ራሱንም ጭምር ለመሸጥ ዝግጁ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው የሐዋርያነት ክብርና ሥልጣን ለእርሱ ምኑም ነው። ዋናው ገንዘብ ነው። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ያመጣችው ሽቱ ተሸጦ ለድኾች እንዲሰጥ ሐሳብ አቀረበ። አልተሳካለትም። የሽቱው ዋጋ 300 ዲናር ነበር። ቢሸጥ ኖሮ ከዐሥር አንዱን 30 ብር ያገኝ ነበር። ያ ሲቆጨው ነው የኖረው። ዲያብሎስ የተጠቀመበት ይሄን ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ ፍላጎቱን ነው። በዚህ የተነሣ ክርስቶስን በ30 ብር ለመሸጥ ተስማማ።

የአይሁድ ጥያቄ ደግሞ የጥቅም ጥያቄ ነው። ለብዙ ዘመናት ሕዝቡን እየበዘበዙ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። እነርሱ ብቻ ዐዋቂና ፈራጅ ሆነው ሲጠቀሙ ኖረዋል። አሁን ለድኾች የሚያስብ፣ ከኃጢአተኞችና ከምስኪኖች ጋር የሚውል፤ ለደካሞች የሚራራ፤ ለሰው ልጅ ክብር ሲል የራሱን ክብር የሚተው መምህርና ጌታ መጣባቸው። ሕዝቡ የሚጠቅመውን ዐወቀ። በዘርና በቋንቋ፣ በአኗኗርና በሀብት ተለያይተው የነበሩትን አንድ አደረጋቸው። ሰው የአይሁድን ካህናት መከተሉን ትቶ ክርስቶስን ተከተለ። ይህ ነገር ጥቅማቸውን ነካው። በዚህ ምክንያት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር መተባበርን መረጡ።

ሮማውያን በዚያን ጊዜ መካከለኛው ምሥራቅን በቅኝ ይገዙ ነበር። አይሁድ ሮማውያንን በጠላትነት ነበር የሚያዩዋቸው። ነጻነታቸውንና ማንነታቸውን የቀሟቸው ጠላቶቻቸው ናቸው። ሮማውያን በሕዝቡ ላይ አያሌ ግፎችን ፈጽመዋል። የአይሁድ ካህናት ግን ከክርስቶስ ይልቅ ገራፊዎቻቸውንና አሣሪዎቻቸውን መረጡ። ሮማውያን በክርስቶስ ላይ የተነሡበት ዓላማቸው የሥልጣን ጥያቄ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ የነጻነትን ወንጌል አስተማራቸው። አዲስ ሕይወትና አዲስ መንገድ ነው አሳያቸው። ይህ የሮማውያንን ሥልጣን የሚነቀንቅ መስሎ ተሰማቸው። ስለዚህም ከአይሁድ ጋር ተባበሩ።

ከሁሉም ኋላ ሆኖ የጥፋት ወጥመዱን የሚያጠምደውና፣ የጥፋት መንገዱን የሚያዘጋጀው ዲያብሎስ ለሦስቱም የሚፈልጉትን እየነገረና እያሳየ፣ ሦስቱንም ለራሱ የጥፋት ዓላማ አሠማራቸው። እነርሱ ግን ለየራሳቸው ዓላማ የሠሩ መስሏቸው ነበር። የዲያብሎስ ዕቅዱ የርሱን ዓላማ አሳክቶ እነርሱ አጨብጭበው እንዲቀሩ ማድረግ ነው። ይሁዳ እየመራ፣ የአይሁድ ካህናት ሕዝቡን አሳምጸውና ሽብር ፈጥረው፣ ሮማውያን ደግሞ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በክርስቶስ ላይ ይሙት በቃ ፈረዱ። እርሱም በመስቀል ተሰቅሎ ሞትን ተቀበለ።

የትንሣኤው ብርሃን የላኪውንም የተላላኪዎቹንም ተንኮል አፈረሰው። ወጥመዳቸውንም በጣጠሰው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስናና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። የዲያብሎስና የሦስቱ የጥፋት ተላላኪዎች ተንኮል የተሳካው ለሦስት ቀናት ብቻ ነው። ይሁዳም 30 ብሩን ሳይጠቀምበት ታንቆ ሞተ። የአይሁድ ካህናትም እንኳንስ ሊሳካላቸው በ70 ዓመተ ምሕረት ሀገራቸውን ጥለው ለሺ ዓመታት ተሰደዱ። ሮማውያንም ቀስ በቀስ ግዛቶቻቸውን እየለቀቁ ዛሬ የደረሱበት ደረሱ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዛሬም አለ። የትንሣኤው በዓል ይሄንን ነው የሚመሰክርልን።

ይሄን ነገር በሀገራችን በኢትዮጵያ አንጻር መመልከቱ መልካም ነው። ዛሬም ከኋላ ሆኖ ሀገራችንን ለማፍረስ ወጥመድ የሚያጠምድ፣ ተንኮል የሚሠራው ጠላት ማነው? ዓላማው ይህችን ሀገር ማጥፋት ብቻ የሆነ፤ ሊያጠፋን እንጂ ሊወዳጀን የማይፈልገው ጠላት ማነው? ምንም ብናደርግለት ይህችን ሀገር ካላጠፋ በቀር የማይረካው ማነው? ይህ ጥንተ ጠላት የሚያሠማራቸው የጥፋት ተላላኪዎቹስ እነማን ናቸው? አንዳንዶቹ ለገንዘብ፣ ሌሎቹ ለጥቅም፣ ሌሎቹም ለሥልጣን ብለው ከዚህ ጥንተ ጠላት ጋር አብረው የሚሠሩት እነማን ናቸው? እነዚህ የጥፋት ተላላኪዎች የራሳቸውን ፍላጎትና ዓላማ የሚያሳኩ መስሏቸው ይሆናል። ካሳኩም የሚያሳኩት እነርሱን ጭምር ሊያጠፋቸው የሚፈልገውን የኢትዮጵያን ጥንተ ጠላት ፍላጎት ብቻ ነው።

ይሁዳም ከሥሯል፤ የአይሁድ ካህናትም ከሥረዋል። ሮማውያንም ከሥረዋል። የጥፋት ተላላኪዎች መጨረሻ እንደዚህ ነውና። ለጊዜው የማይገናኙ ተገናኝተው፤ የማይተባበሩ ተባብረው፤ አጥፊና ጠፊ ተወዳጅተው፣ በክርስቶስ ላይ ሲነሡ፤ ለጊዜው የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር። መጨረሻው ግን ኪሣራ ነው። ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሡ ሁሉ ለጊዜው የሚሳካላቸው ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻቸው ኪሣራ ነው። ጥቂት ቀናት የተሳካላቸውና ያሸነፉ ቢመስላቸውም ኢትዮጵያ ሞተው እንደሚቀሩ ሀገራት አይደለችም። ከሙታን ትነሣለች። ጠላቶቿንም ታሳፍራለች። አሳፍራም ታከሥራለች።

በድጋሜ መልካም የትንሣኤ በዓል!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዚያ፣ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.[ad_2]

Source link

What do you think?

Aggregated by Ethiopian News Digest

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

GIPHY App Key not set. Please check settings

Waldaan Hawaasa Oromoo Minisootaa gochaa mootummaan Itoophiyaa Oromoo fi Oromiyaa irratti raawwataa jiru cimsee balaaleffate. – OMN

59th Venice Biennale One Stop Guide To Artists Curators And Pavilions-Artlyst