in

ቅዱስ ቁርኣን በአማርኛ ሲተረጎም (1961) || ጸሐፊ አፈንዲ ሙተቂ

[ad_1]

ቅዱስ ቁርኣን በአማርኛ እንዲተረጎም ትዕዛዝ ያስተላለፉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ነበሩ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ትእዛዙን ያስተላለፉት ሐምሌ 18/1958 በተጻፈ ደብዳቤ ነበር። የንጉሡን ደብዳቤ በመንተራስ ስራው እንዲጀመር ያደረጉት ደግሞ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ምናሴ ሃይሌ ናቸው፡፡ ዶ/ር ምናሴ በተርጓሚነት የመረጡት ከአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የሚታተመው የ“አል-ዐለም” ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን ይሰሩ የነበሩትን ሐጂ በሺር ዳውድን ነው (ሐጂ በሺር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የተገነባው ትልቅ መስጂድ ኢማም ነበሩ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዳረፉ ሰምቻለሁ፤ አላህ ይርሓማቸው)፡፡

ሐጂ በሽር ከዶ/ር ምናሴ የተሰጣቸውን አመራር በግርድፉ አልተቀበሉትም፡፡ “ቁርኣንን መተርጎም ሌሎች መጽሐፍትን እንደ መተርጎም ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ ኮሚቴው በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ነው መሰራት ያለበት” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ አባባላቸው ተቀባይነት በማግኘቱም የቁርኣን ትርጉም ኮሚቴው ተዋቀረ፡፡ ከሀገር አቀፉ ኮሚቴ አባላት መካከል እንደርሳቸው የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የነበሩት ሼኽ ዓብዱል ከሪም ኑርሑሴን ይጠቀሳሉ።

ኮሚቴው የትርጉሙን ስራ በብቃት ማከናወን የሚችሉ ዓሊሞችን ማፈላለግ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ትልቁ ችግር የነበረው በእስላማዊ እውቀትም ሆነ በዓለማዊ ትምህርቱ ብቁ የሆነ ዓሊም ማግኘት ነበር፡፡ በተለይም አማርኛ ቋንቋን አስተካክሎ ከመጻፍ ጀምሮ የቋንቋውን የሰዋስው እና የስነ-ልሳን ህግጋትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዓሊም ማግኘቱ አስፈላጊ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ዓሊሞቻችን የመጀመሪያውን መስፈርት ቢያሟሉም የኋለኛው ይጎድላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ኮሚቴው በሓጂ በሺር ዳውድ ጠቋሚነት ሁለት ሰዎችን አገኘ፡፡ እነርሱም በጊዜው በደሴ ከተማ በሚገኘው የወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ እና የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ ነበሩ፡፡ በዚህ መሰረት ሁለቱ ዓሊሞች ዋና ተርጓሚ ሆነው ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ሓጂ በሺር ዳውድ እና ሼኽ ዐብዱል ከሪም ኑርሑሴን ደግሞ ተባባሪ ኤዲተሮች ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡

ተርጓሚዎቹ ከኤዲተሮቹ ጋር በቅርበት እየሰሩ በአስራ አምስት ወራት ውስጥ ስራቸውን አጠናቀቁ፡፡ ሆኖም ከየክፍለ ሀገሩ የተመረጡ ዑለማ የትርጉሙን ረቂቅ አንብበው የእርማትና የማሻሻያ ሓሳቦችን እንዲሰጡበት ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ተሰነዘረ፡፡ በዚሁ መሰረት የሚከተሉት ታላላቅ ዑለማ ወደ ኮሚቴው ቀርበው ረቂቅ ስራውን በማንበብ ሃሳባቸውን እንዲሰጡበት ተደረገ፡፡

ሼኽ ቡሽረል ከሪም ሙስጠፋ (ከወሎ)
ሓጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን ገራድ (ከሀረርጌ)
ቃዲ ሙሐመድ ዐብዱራሕማን (ከትግራይ)
ሓጂ አሕመድ ዳለቲ (ከሸዋ)
ሓጂ መንዛረሁ ከቢር ሑሴን (ከአርሲ)

በመጨረሻም ተርጓሚዎቹ ከአምስቱ ዑለማዎች የተሰጡትን አስተያየቶችና ሌሎች የማሻሻያ ሃሳቦችን በመቀበል ረቂቁን አርመው አዘጋጁ፡፡ አሁን በእጃችን ላይ የሚገኘው የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉምም በ1961 የመጀመሪያ ወራት ውስጥ ለህትመት በቃ፡፡
—–
ያ የቁርኣን ትርጉም በዚህ ዘመን እየወጡ ካሉት የአማርኛ ትርጉሞች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ አንድ ሰው ከቁርኣን ፍቺ ከሚያገኘው መልዕክት በተጨማሪ የዐረብኛ ሰዋስውን ባህሪ ለማወቅ ካሻው ከዚያ የትርጉም ስራ ብዙ ቁም ነገሮችን ይማራል፡፡ ለምሳሌ እኔ አፈንዲ በዐረብኛ የሚታወቁትንና በአማርኛ ውስጥ የሌሉትን የአገናዛቢ አጸፋ ተውላጠ ስሞችን አጠቃቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ከዚያ የቁርኣን ትርጉም መሆኑን እመሰክራለሁ፡፡ ለዚህም አንድ አብነት ብቻ ልስጣችሁ፡፡ ዐረብኛው “ዛሊከ” ሲል “ይህ” ማለት ነው፤ ይህንኑ ተውላጠ ስም ወደ ብዙ ቁጥር ስንቀይረው “ዛሊኩም” ይሆናል፤ ይህም በአማርኛ ሲፈታ “ይሃችሁ” እንደማለት ነው፤ እንዲህ ዓይነት አነጋገር በአማርኛ ሰዋስው ውስጥ ባይታወቅም በዚያ የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ውስጥ በደንብ ታያላችሁ፡፡

ደግሞ ሌላ መሰረታዊ ቁምነገር ይኸውላችሁ፡፡ በአማርኛ “አጎት” ከተባለ የእናት ወይም የአባት ወንድም ማለት ነው፡፡ “አክስት” ከተባለ ደግሞ የእናት ወይም የአባት እህት ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛም ሁለቱን አጎቶች uncle እንላቸዋለን፡፡ ሁለቱን አክስቶች ደግሞ aunt ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ በዐረብኛ፤ በኦሮምኛ፣ በሀረሪ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ግን ሁለቱ አጎቶች እና ሁለቱ አክስቶች በተለያዩ ስሞች ነው የሚጠሩት፡፡ በዐረብኛ የእናት ወንድም የሆነው አጎት “ኻል” ነው የሚባለው፡፡ የእናት እህት ደግሞ “ኻላህ” ትባላለች፡፡ የአባት ወንድም “ዓም” የሚባል ሲሆን የአባት እህት “ዓምማህ” ትባላለች፡፡ እንግዲህ ቁርኣን በዐረብኛ የወረደ እንደመሆኑ ሁለቱን አጎቶች “ኻል” እና “ዓም” እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡ ሁለቱ ሰዎች በአማርኛ ቋንቋ በአንድ ዘርፍ “አጎት” ተብለው ከተጠሩ የቁርኣን ፍቺ የተዛባ ሊሆን ነው ፡፡ለምሳሌ በእስልምና አስተምህሮ መሰረት “ኻል” እና “ዓም” እኩል የወራሽነት ድርሻ የላቸውም፤ በመሆኑም ሁለቱ ሰዎች “አጎት” ተብለው ከተጠሩ ይህንን ልዩነት ማስገንዘብ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡

ተርጓሚዎቹ ይህንን ክፍተት ለመሙላት “አሪፍ” ቀመር ነው የተጠቀሙት፡፡ ይህም በወሎ ከሚነገረው የደዌ ኦሮምኛ ዘዬ ተጨማሪ ቃላትን መበደር ነው፡፡ በዚህም መሰረት በዚያ የአማርኛ የቁርኣን ፍቺ ውስጥ “አጎት” ማለት የአባት ወንድም ብቻ ነው፡፡ የእናት ወንድም ደግሞ “የሹማ” ተብሎ ነው የሚጠራው (የደዌ ኦሮሞዎች ናቸው እንዲህ የሚሉት፤ ሌላው ኦሮሞ “ኤሱማ” ነው የሚለው)፡፡ የአባት እህት “አክስት” የተባለች ስትሆን የእናት እህት ደግሞ “የሹሜ” ተብላ ተሰይማለች፡፡ በዚህ ዓይነት ዘዴ የቁርኣኑን የዐረብኛ መልዕክት ያለምንም ችግር ወደ አማርኛ ለመመለስ ተችሏል፡፡

በቅዱስ ቁርኣኑ ፍቺ ውስጥ አጽንኦት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የድምጾችና የፊደላት ውክልና ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዐረብኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ውስጥ ያሉ በርካታ ድምጾችን በአማርኛ ውስጥ አናገኛቸውም፡፡ በአማርኛ “አ” እና “ዐ” እየተባለ ቢጻፍም ሁለቱን ፊደላት ያለምንም የድምጽ ልዩነት ነው የምናነባቸው፡፡ በግዕዝና በትግርኛ ቋንቋዎች ግን ሁለቱ ፊደላት የተለያዩ ድምጾችን ነው የሚወክሉት፡፡

ዐረብኛም “የአንድ ፊደል ለአንድ ድምጽ” መርህን የሚከተል በመሆኑ በጽሑፍ ጊዜ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ተርጓሚዎቹ ቁርኣንን በአማርኛ ሲፈቱት በተለይ የተጸውኦ ስሞች በኦሪጂናሌው ድምጽ መጠራት እንዳለበት አምነዋል፡፡ በመሆኑም በትርጉም ስራው ውስጥ ያሉት የተጸውኦ ስሞች ይህንን መርህ በመከተል ነው የተጻፉት፡፡ ለምሳሌ በትርጉሙ ውስጥ “ያሕያ” እንጂ “ያህያ” የሚል ስም አታገኙም (“ሐ” ቀጭኑንና በጉረሮ የሚነገረውን የዐረብኛውን “ሐእ” ነው የሚወክለው፤ ሃሌታው “ሃ” ደግሞ “ዋው” ከተሠኘው የዐረብኛ ፊደል አጠገብ የሚገኘውን ወፍራሙን “ሀ” ነው የሚወክለው)፡፡ የመርየም ልጅም “ዒሳ” እንጂ “ኢሳ” ተብሎ አልተጠራም፡፡ “ዒስማኢል”፣ “ኢብራሂም”፣ “አዩብ”፣ “ኢስሓቅ”፣ “ያዕቁብ”፣ ወዘተ… አሁን በጻፍኩት መልኩ ነው የተጠሩት፡፡

ከዚህ ሌላ ተርጓሚዎቹ በጥንታዊው ዐረብኛ ያሉትን ቃላት ለመጥራት ሲሉ ከየገጠሩ የሰበሰቧቸው የአማርኛ ቃላት በጣም ያስድምማሉ፡፡ ለምሳሌ “ዘለበት”፣ “ቀንዘል”፣ “እንዛዝላ”፣ “ሰርክ”፣ “አጎበር” የመሳሰሉ ቃላትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ከዚሁ የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች በሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሷዲቅ እና በሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ የተዘጋጀው የቁርኣን ትርጉም ይከብደናል ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ያለውን መቅድም ስለማያነቡት ይመስለኛል ፍቺው ከበደን የሚሉት፡፡ መቅድሙን በአትኩሮት ያነበበ ሰው ግን ምንም ግራ የሚገባው አይመስለኝም፡፡
—-
እነዚያ ዑለማ ቅዱስ ቁርኣንን በአማርኛ የተረጎሙልን የእስልምና መጻሕፍትን በሀገራችን ቋንቋዎች ማዘጋጀት በማይታወቅበት የጭለማ ዘመን ነበረ፡፡ ዛሬ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች እስልምናን በማስተማር ስም የነዚያን ደጋግ አባቶቻችንን መልካም ስራ ሊያጠለሹት ሲሞክሩ ሳይ በእጅጉ ይደንቀኛል፤ ይገርመኛልም፡፡ የፓምፍሌትና እና የብሎግ ጽሑፎችን ከማንበብ ያልበለጠ እውቀት ያለው ሰው ሌሎችን የመፈረጅን ድፍረት ከየት እንዳመጣው ማወቁም የማይቻለን ሆኗል፡፡ በመሆኑም ሁሉንም ለአላህ ትቶ ማለፉ ይመረጣል፡፡

በእኛ በኩል ግን በትርጉም ስራው ላይ በተሳተፉት ዑለማዎቻችን መካከል አንዳች ልዩነት ሳናደርግ መልካም ስራቸውን እንዘክርላቸዋለን፡፡ ሁለቱ ተርጓሚዎች፤ ሁለቱ ኤዲተሮችና ከየክፍለ ሀገሩ የተመረጡት አምስቱ አራሚዎች በሙሉ ባለውለታዎቻችን በመሆናቸው ዘወትር እናስታውሳቸዋለን፡፡ አላህ የበጎ ስራቸውን ምንዳ በጀንነት ይክፈላቸው፡፡ አሚን!!
——
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ታሕሳስ 22/2007 ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ሰኔ 17/2007 ተጻፈ፡፡
ሀረር
ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ
——-
የትረካ ምንጮች
1. ቅዱስ ቁርኣን፡ የአማርኛ ትርጉም በሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፣ 1961፣ አዲስ አበባ
2. “ቢላል መጽሔት”፡ ቅጽ 1፡ ቁጥር 9፡ ግንቦት 1985
3. ቢላል መጽሔት፡ ቅጽ 1፡ ቁጥር 11፡ ሐምሌ 1985
4. ልዩ ልዩ ቃለምልልሶች[ad_2]

Source link

What do you think?

Aggregated by Ethiopian News Digest

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

GIPHY App Key not set. Please check settings

DPM & FM Demeke Lauds Initiative of Israeli MPs, Medical Professionals

Kaayyoo Gootonni Oromoo wareegamaniif fiixa ni baafna jedhe WBOn. – OMN